Thursday, June 27, 2013

የፌዴሬሽኑ ቅሌት ሊያስከስስ ይችላል ተባለ

  • ጉዳዩ የቡድን መሪውንና አሰልጣኙን ተጠያቂ እንደሚያደርጋቸው ተገለፀ
  • ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ ከ6 ወር እስከ 10 አመት በእስር ሊቀጡ ይችላሉ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለአለም ዋንጫ ማጣሪያ ከደቡብ አፍሪካ አቻው ጋር ተጫውቶ ያስመዘገበው ሶስት ነጥብ በፊፋ ውሳኔ መቀነሱን ተከትሎ ብዙዎችን እያነጋገረ ያለው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስህተት፣ በወንጀልና በፍትሀብሔር ህግ ያስጠይቃል ሲሉ የህግ ባለሙያዎች ተናገሩ፡፡ በወንጀል ህጉ አንቀጽ 702 እና 703 ላይ የተረከቡትን ስራ በአግባቡ አለመወጣት እና ቸልተኝነት ወይም አውቆ አለማድረግ እንደሚያስከስስ የተናገሩት የህግ ባለሙያው አቶ ፈቃዱ ፀጋ፤ የቡድን መሪው እንደተባለው ከጉዳዩ ጋር የሚያያዘው ደብዳቤ ደርሶት ተገቢውን እርምጃ ሳይወስድ ከቀረ ሃላፊነቱን ባለመወጣት ተጠያቂ ይሆናል ብለዋል፡፡
አሠልጣኙም የስራ ዝርዝር ሃላፊነታቸው ላይ የተቀመጠውን ነገር በአግባቡ ካልፈፀሙ ተጠያቂ ይሆናሉ የሚሉት አቶ ፍቃዱ፤ በወንጀለኛ ህጉ አንቀፅ 58 1 (ሀ) እና (ለ) “ቀጥታ ቸልተኝነት” ወይም ደግሞ “የሆነ ይሁን ብሎ” የሚል ሲሆን፣ ሃላፊው “የሆነ ይሁን” ብሎ፣ “ቅጣት ቢመጣም ይምጣ” በሚል ማሳለፍ ፈልጐ ካደረገ ወይም የተቀጣን ለይቶ ማሰለፍ ሲገባው ባለማድረጉም ለሰራው ስራ ሁለቱም በዚህ አግባብ ሊጠየቁ እንደሚችሉ ገልፀዋል፡፡ ይሄ አንቀጽም ከ 6ወር -10 አመት የሚያስቀጣ መሆኑን ገልፀው፤ ከዚህ በኋላም አገሪቱ ያጣችውን በፍትሀብሔር መጠየቅ ትችላለች ብለዋል፡፡ ሌላው የህግ ባለሙያ አቶ ደበበ ኃ/ገብርኤል በበኩላቸው፤ በጉዳዩ ሰበብ የሚደርስ በገንዘብ የሚተመን ጥቅም ከቀረ ሙያዊ ሀላፊነት በአግባቡ ባለመወጣት እና በአስተዳደራዊ እርምጃ ሊጠየቁ ይችላሉ ብለዋል፡፡
የገንዘብ ጥቅምን በተመለከተ በፍትሐብሔር መጠየቅ ይቻላል የሚሉት አቶ ደበበ፤ አስተዳደራዊ እርምጃን በተመለከተም ከስራ ማሰናበትና ሌሎች አስተዳደራዊ እርምጃዎችን መውሰድን እንደሚያካትት ገልፀዋል፡፡ ድርጊቱ የተፈፀመው በከፍተኛ ቸልተኝነት ከሆነ ደግሞ በወንጀል ሊጠየቁ ይችላሉ ያሉት አቶ ደበበ፤ በሚከሰሱበት የወንጀል አይነቶች እንደየደረጃቸው ሊቀጡ እንደሚችሉም ተናግረዋል፡፡ የተሰጠን ሃላፊነት በቸልተኝነት አለመፈፀም ብቻ ሳይሆን ለመፈፀም ያልቻሉበት ሁኔታ ምንድነው የሚለውን በዋናነት በማየት አሳማኝነቱ ተመዝኖ የቅጣቱ ክብደትና ማነስ እንደሚታወቅም አክለዋል - የህግ ባለሙያው፡፡

No comments:

Post a Comment